የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በቀንና በማታ መርሐ-ግብር ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመረቀ፡፡ ሀምሌ 10/2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሰንዳፋየኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በመደበኛ ዲፕሎማ ፣ በድህረ-ምረቃ ዲፕሎማ ፣ በጤና ዲፕሎማ በዲግሪ እና ለመጀመሪያ ጊዜ በስነ-ወንጀል እና የወንጀል ፍትህ በሁለተኛ ዲግሪ (ማስተር ) መርሀግብር ያስተማራቸውን 465 ሠልጣኝ መኮንኖችና ዕጩ መኮንኖችን በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመርቋል፡፡በምረቃ ፐሮግራሙ ላይ ክብርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬአለም ሽባበው ፣ የኢፌዴሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፣ ሚኒስቴር ዴታዎች ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ፣ከፍተኛ የመከላከያ እና የፖሊስ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡”ውድ የዛሬ ተመራቂዎች ላለፉት አመታት በትምህርትና ስልጠና ቆይታችሁ በህይወታችሁ እልህ አስጨራሽ ስልጠና እንደነበር ለመገመት አያዳግትም ፡፡ ይህን እልህ አስጨራሽ ጊዜ አሳልፋችሁ ለዚህ ክብር መብቃት ደግሞ ሌለኛው አንፀባራቂ ድል በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ” ያሉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊስ ሰራዊት አቅም በትምህርትና በስልጠና በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ድረሻ ያለው በመሆኑ በየጊዜው የትምህርትና ስልጠና አድማሱን በማስፋት በአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የፖሊስ የምርምር ትምህርት ተቋም ሆኖ መገኘት ይገበዋል ብለዋል፡፡የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸው “በዛሬው ዕለት በልዩ ልዩ ትምህርትና ስልጠና መስኮች የምትመረቁ እና ይህንን ቀን በጉጉት ስትጠብቁ ለነበራችሁ ሁሉ እንኳን ለዚች ታላቅ የምረቃ ቀን አበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ፡፡ ኮሚሽነር ጀነራሉ በዚሁ አያይዘው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአንድ በኩል ተቋማዊ ሪፎርም በማካሔድ ወደ ትግበራ በገባበት በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በመከላከል የህግ የበላይነትን ለማስከበር በጀግንነት እየመከተ ባለበት ወቅት ላይ መመረቃችሁ ምረቃቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ በአፍሪካ ከሚገኙወዳጅ ሀገራት በፖሊስ ትምህርት ና ስልጠናዎች ተደራሽ ለማድረግ እና በቀጠናው ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም በጋራ የመበልፀግን አስተሳሰብ ለማምጣት ዩኒቨርሲቲው ለደቡብ ሱዳን ፣ ከሱማሌ እና ከጅቡቲ ለሚመጡ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት ዝግጅት መጨረሱን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ም/ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ ገልፀዋል፡፡